መደበት/ Depression…..ጠቃሚ ነውና ለወዳጅዎችዎ ያካፍሉ።

ጤና ይስጥልኝ ወዳጆቼ ለዚህ ሳምንት ለእናንተ ይበጃሉ የምላቸውን ጤና ነክ ጉዳዮች እጽፍላሁኣለሁ። ጠቃሚ ነውና ለወዳጅዎችዎ ያካፍሉ።

መደበት/ Depression
(በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም)

መደበት የሚባለው የባሕርይ መለወጥን የሚያስከትል የሕመም ዓይነት ሲሆን የመከፋት፤ደስተኛ ያለመሆን እና ፍላጎት የማጣት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡

እነዚህ ስሜቶች የዕለት ተዕለት ኑሮአችንንና ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሊጎዱ ወይንም ችግር ሲያስከትሉ የመደበት ሕመም / Depression ብለን እንጠራዋለን፡፡

በዚህ ሕመም የሚጠቁ ሰዎች በሕክምና ባለሙያ በሚደረግ የምክር አገልግሎት ወይንም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን በትክክል በመውሰድ ከሕመሙ ሊድኑ ይችላሉ፡

► ለሕመሙ ተጋላጭነት የሚዳረጉ ሁኔታዎች

በአብዛኛው የመደበት ስሜት መሰማት የሚጀምረው በወጣትነት ዕድሜ ላይ ሲሆን በ20 እና በ30ዎች ዕድሜ ላይ ይበረክታል፡፡ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች፡-

 በልጅነት የጀመረ የመደበት ስሜት

 መጠጥ እና አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች

 በራስ የመተማመን የሌላቸው፤ አሉታዊ አስተሳሰብ የሚያዘወትሩ

 ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ሕመም ያላቸው እንደ ካንሰር፤ስኳር ወይንም የልብ ሕመምተኞች

 በሕይወት ዘመን የደረሰ መጥፎ አጋጣሚ ወይንም ክስተት ወዳጅ ወይንም የቤተሰብ አባል የሞተበት ሰው፤መደፈር የደረሰበት ሰው፤በፍቅር ግንኙነት የተጎዳ ሰው ወይንም የገንዘብ ችግር ያጋጠመው ሰዉ

 በዘር ውስጥ ተመሳሳይ ሕመም ያለው ሰው መኖር ናቸው፡፡

► የህመሙ ምልክቶች

 ንዴት፤መነጫነጭ፤የሀዘን ስሜት መሰማት(መከፋት) ባዶነት መሰማት

 ከዚህ በፊት የሚያስደስቱንን ነገሮች መጥላት (ፍላጎት ማጣት)

 እንቅልፍ ለመተኛት መቸገር ወይንም እጅግ ብዙ መተኛት

 ድካም መሰማት ትናንሽ ሥራዎችን ለመስራት መቸገር

 የምግብ ፍላጎት ማጣት አንዳንድ ሰዎች ላይ የምግብ ፍላጎት መጨመር

 ጭንቀት፤ዕረፍት ማጣት

 የቀሰሰ አስተሳሰብ፤ንግግርና የሰውነት እንቅስቃሴ

 ጥፋተኝነት እና ዋጋቢስነት መሰማት፤ራስን መውቀስ

 ትኩረት ለመስጠት፤ለማሰብ እና ውሳኔ ለመስጠት መቸገር

 በአብዛኛው ስለሞት ማሰብ፤እራስን ለማጥፋት ማሰን እና መሞከር

 የተረጋገጠ መንስኤ የሌላቸው አካላዊ ሕመምች መሰማት የራስ ምታት እና የጀርባ ሕመም የመሳሰሉት ናቸው፡፡

የመደበት ስሜት የሚሰማዎ ከሆነ ወደ ሐኪም በአፋጣኝ መሄድ ተገቢ ነው፡፡ መደበት ሕክምና ካላገኘ እየባሰ ሊሄድ የሚችል የሕምም ዓይንት ነው፡፡ ሕመሙን ያልታከመ ሰው ለሌላ ለከፋ የአዕምሮ እና አካላዊ ሕመም የመዳረግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

የከፋ የመደበት ስሜት እራስን እስከማትጥፋት ስለሚያደርስ ችላ ሊባል አይገባም፡፡
ወደ ሕክምና መሄድ የማይፈልጉም ከሆነ ለሚቀርቡት ሰው፤ለጓደኛ ወይንም ለሐይማኖት አባቶች ስለሚሰማዎ ስሜት ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡

► የመደበትን ስሜት ለመከላከል

 አስጨናቂ ነገሮችን ለመውጣት በራስ የመተማመን ስሜት ማዳበር

 የቤተሰብ አባልን ወይንም የቅርብ ጓደኛን ማማከር

 የመደበት ስሜት ሲሰማዎ በአፋጣኝ ወደ ሐኪም በመሄድ ሁኔታው እንዳይባባስ ማድረግ

 ሕመሙ ተመልሶ እንዳያገረሽ ከሐኪምዎ ጋር ዘላቂ መፍትሔ ላይ መወያየት

ጤና ይስጥልኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *