ቆዳን ጤናማ አድርጎ ለመቆየት የሚያስችሉ ምክሮች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቆዳ የሰውነታችን ትልቁ አካል እንደመሆኑ የሰውነታችንን ጤናማነት ለመጠበቅ ሚናው ከፍተኛ ነው።

ቆዳ የህይወታችንን ታሪክ የሚገልፅ በመሆኑም እድሜያችን እና ጤንነታችን በቆዳችን ይንጸባረቃል ሲሉ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።

በተጨማሪም የሰውን ውጫዊ አካል ከባክቴሪያዎች፣ ከቫይረሶች፣ ከአየር ብክለት እና ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ለመከላከል ይረዳል።

ቆዳ የሰውነት ሙቀትን እና እርጥበትን ይቆጣጠራል፤ ጎጂ የፀሐይ ብርሃን ጨረሮችም ይከላከላል።

ይሁን እንጂ እንደ እርጅና፣ የሆርሞኖች ሁኔታ እና እንደ ስኳር በሽታ ያሉ ሁኔታዎች በቆዳ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውስጣዊ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለመኖር፣ ድርቀት፣ ማጨስ እና በተለይ መድሃኒቶች በቆዳዎ ላይ ተጽእኖዎች ሊያሳድሩ የሚችሉ ናቸው።

ታዲያ ቆዳዎ ይህን ያክል ጠቀሜታ እንዳለው ካወቁ፥ ቆዳዎን ሙሉ ጤንነት ኖሮት የለስላሳነት ባህሪውን ጠብቆ እንዲዘልቅ የሚሰጡ ምክሮች አሉ።

1. ጤናማ አመጋገብ ይኑርዎት

አሁን ላይ ግዙፍ ኩባንያዎች የቆዳን ልስላሴ የሚጠብቁ የተለያዩ የቅባት ዓይነቶችን አቅርበው ለገበያ ያቀርባሉ።

ሆኖም እነዚህ ቅባቶች ቆዳን እና የተወሰነ የውስጥ ክፍሉን ልስላሴ እና ጤንነት ይጠብቁ ከሆነ እንጂ ሙሉ በሙሉ ከውስጥ በሆነ መልኩ የቆዳን ጤንነት ለመጠበቅ እና ልስላሴን ለማጎናፀፍ አያስችሉም።

ይህን ሊያደርግልን የሚችለው የምንመገበው ምግብ ነው የሚሉት ተመራማሪዎች፥ ይህን የሚያደርጉ የምግብ ዓይነቶችን ያስቀምጣሉ።

ከሚመከሩት ምግቦች መካከል አንዱ የሆነው ማንጎ የቆዳን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ንጥረ ነገር እንደያዘ ያስረዳሉ።

ቲማቲም፦ የቆዳ ካንሰርን የመከላከል አቅም አለው። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በየዕለቱ ቲማቲም ከሌሎች የምግብ ዓይነቶች ጋር ቀላቅለው የሚመገቡ ሰዎች ለፀሀይ ብርሃን ከመጋለጥ የሚመጣው የቆዳ ካንሰር እብጠት እድገትን በ50 በመቶ መቀነስ አስችላቸዋል።

001.jpg

የወይራ ዘይት፦ የረጅም ጊዜ የፀሐይ ብርሃን መጋለጥን ተከትሎ በቆዳ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ጨምሮ የፊት ገፅ ላይ የሚታዩ ጥቁር ነጠብጣቦች፣ መቦርቦር እና ቀለም መቀያየር ጉዳቶች መከላከል ያስችላል።

በቾኮሌት ውስጥ የሚገኙ የኮኮዋ ፍላቫኖል(flavanols)የቆዳው መዋቅር እና ተግባር ሊያሻሽሉ ይችላሉ። ተመራማሪዎቹ ኮኮዋ ፍላቫኖል ጣፋጭነት፣ ቆዳ ሸካራነቱ እንዲቀንስ እንዲሁም የፀሐይ ጨረር እንዳይጎዳው የማድረግ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በአረንጓዴ ሻይ፣ ነጭ ሻይ፣ የአሳ ዘይት፣ አኩሪ አተር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችም የቆዳ ጤንነት በመጠበቅ ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል ያግዛሉ።

2. ራስን ከውጥረት መጠበቅ

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከፍተኛ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች በቆዳቸው ጤንነት ላይ መጓደል ተስተውሏል። ቆዳን ማሳከክ፣ የፀጉር መርገፍ፣ የቆዳ ማፈክፈክ፣ ከፍተኛ ላብ እና የእጅ ሽፍታ ታይቶባቸዋል።

በተጨማሪም ጥናቶች፥ ከፍተኛ ጭንቀት ካለባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች 23 በመቶ የሚሆኑት በፊታቸው ከፍተኛ የሆነ እብጠት ሊኖራቸው እንደሚችሉ አመልክቷል።

02.jpg

ስለዚህ ጭንቀትዎን መቀነስ ጤናማ ቆዳ እንዲኖርዎ ያደርጋል።

3. የቆዳ ውስጥ እርጥበትን መጠበቅ

የቆዳ እርጥበት መጠበቅ የላይኛውን የቆዳ ሴሎች ድርቀት ለመከላከል ይረዳል።

የአሜሪካ የቆዳ ህክምና አካዳሚው የቆዳ እርጥበትን በመጠበቅ ድርቀትን ለመከላከል፣ የቆዳ ቅላት እና የቆዳን ማሳከክ ለመከላከል የሚከተሉትን መንገዶች ይመክራል።

በየቀኑ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ሰውነት መታጠብ የቆዳውን ቅባት ሊያጠፋና ሊያደርቀው ይችላል።

ሰውነትዎ ወይም ፊትዎን ሲታጠቡ ሙቅ ውሃ ሳይሆን የቀዘቀዘ ውሃን ይጠቀሙ።

ደረቅ ሳሙናዎችን ከመጠቀም ይልቅ ልስላሴ ያለው ይጠቀሙ።

03.jpg

በቆዳው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የጥርስ ብሩሽዎች፣ የውሃ ስፖንጅ እና የእጅ መታጠቢያዎችን ያርቁ።

ከታጠቡ በኋላ ወዲያውኑ የቆዳዎን እርጥበት ለመንከባከብ የሚረዳ ቅባት፣ ሎሽን እና ክሬም በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ መተግበር ያስፈልጋል።

እነዚህ ምክሮችን በመተግበር የቆዳዎ ድርቀት ለውጥ ካላመጣ የቆዳ ባለሙያዎን ቢያነጋግሩ ይመከራል።

4. ማጨስን ያቁሞ

ማጨስ የሰውነት ክፍሎች እና ቆዳን ይጎዳል። ማጨስ በቆዳው ውጫዊ ክፍል ላይ የሚገኙትን የደም ሥሮች በማዳከም የደም ፍሰቱን ይቀንሳል፤ እንዲሁም ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች እና ኦክስጅን እንዲዳከሙ ያደርጋል።

04.jpg

ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ለቆዳዎ ጤንነት ሲሉ ማጨስ ቢያቆሙ ይመከራል።

5. በቂ እንቅልፍ ማድረግ

በቂ እንቅልፍ ማግኘት የቆዳዎ ጤንነት ያስተካክላል።

ብሔራዊ የእንቅልፍ ፋውንዴሽን፥ አዋቂዎች በየቀኑ ከ7 እስከ 9 ሰዓታት በቂ እንቅልፍ ካገኙ ለጤናቸው በተለይ ደግሞ ለቆዳ ጥሩ መሆኑን ይመክራል።

በቂ እንቅልፍ አለመውሰድ ከመጠን ባለፈ ውፍረት፣ በሽታ የመከላከል ችግር፣ የስኳር በሽታ እና ካንሰር ጋር የተቆራኘ ነው።

05.jpg

የእንቅልፍ ችግር በቆዳ ሥራ እና በእድሜው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ጥናቶች ያሳያሉ።

በአጠቃላይ ቆዳዎ ጤናማ ሆኖ ለመቀጠል እነዚህን ምክሮች መተግበር ያስፈልጋል።

ምንጭ፦https://www.medicalnewstoday.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *