#ቲታነስ እንዴት ይከሰታል? እንዳይከሰትብንስ ምን እርምጃ መውሰድ አለብን? መንስኤና መፍትሔ የዛገ ነገር ሲወጋችሁ፣ ፍፁም ችላ አትበሉት

ቲታነስ ወይም መንጋጋ ቆልፍ እንዴት ይከሰታል? እንዳይከሰትብንስ ምን እርምጃ መውሰድ አለብን? መንስኤና መፍትሔ

የመንጋጋ ቆልፍ ወይም የቲታነስ በሽታ የሚመጣው በአፈር፣ በአቧራ ብናኝ፣ በፍግና በብረት ዝገቶች ላይ ከሚገኙ ቆሻሻዎች ውስጥ ከሚኖር ክሎስትሪዲየም ቲታኒ(Clostridium tetani) ከተባለ የባክቴሪያ አባል ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ ከሌሎች ባክቴሪያዎች በተለየ መልኩ ከሰው ልጅ ውጪ መኖሪያ አለው። ባክቴሪያው ለረጅም ጊዜ በአፈር በከብቶች አዛባ ውስጥ የመኖር ባህሪይ አለው። ይህ በሽታ የሚያጠቃው የነርቭ ስርዓትን ሲሆን ሲጠና የጡንቻ አካላት ከፍቃዳችን ውጪ እንዲግተረተሩ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚጀምረው ከመንጋጋ ሲሆን መንጋጋ ቆልፍ የሚለው ስያሜም የመጣው ከዚሁ ነው፤ በመንጋጋችን አካባቢ ያለው ጡንቻችን በሽታው ሲጀምረን ዝግትግት የማለት ባህሪይ አለው። በመቀጠልም ወደሌላው የሰውነታችን ክፍል ይስፋፋል፡፡ ከሰውነት መግተርተር ውጪ ላብ፣ ራስምታት፣ ማንኛውንም ነገር ለመዋጥ መቸገር፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና የልብ ምት የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት በባክቴሪያው ከተለከፍን ከ3-21 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡

የመንጋጋ ቆልፍ ወይም የቲታነስ በሽታ

በሽታው እንዴት ይይዘናል?

ይህ ባክቴሪያ ወደ ሰውነታችን የሚገባበት መንገድ በቁስሎች አማካኝነት፣ ባክቴሪያውን የተሸከሙ የቆሸሹ ስንጥሮች፣ ምስማሮች፣ የተለያዩ ብረቶች፣ መርፌዎችና ሌሎች ቁሶች ሲወጉን ሊሆን ይችላል፡፡ እነኝህ ባክቴሪያዎች በጡንቻ ስርዓት ላይ ጣልቃ የሚገባ ቶክሲን ይለቃሉ ወይም ያመርታሉ፤ በሽታው ከሰው ሰው የሚተላለፍ አይደለም፡፡

የቲታነስ በሽታ የሚይዝበት መንገድ

ሕክምናው ምንድነው?

ዋነኛ ሕክምናው የቲታነስ መድኀን( tetanus toxoid) ክትባት ሲሆን በመርፌ የሚሰጥ ነው፤ የክትባቱ ብርታት እስከ አስር አመት ሊቆይ የሚችል ነው፡፡ እንዲሁም በባክቴሪያው ተለክፈናል የሚል ጥርጣሬ ሲኖር የቲታነስ ኢሚዩኖግሎቡሊን(tetanus antibodies or tetanus antitoxin) በመርፌ መልክ ሊሰጥ ይችላል፤ ይህ ሕክምና የሚሰጠው የሕክምና ባለሙያን በማማከር መሆን አለበት፡፡ በሽታው ስር ከሰደደ ለሕክምና አስቸጋሪና ውስብስብ ነው፤ ሕክምናውን በጊዜ ካላገኘም ገዳይ ነው፡፡

የቲታነስ ክትባት

ማስጠንቀቂያ!

ይህ ባክቴሪያ ህይወት በሌለው ነገር ውስጥ ሕይወት አልባ መስሎ በመጠለል፣ ወደ ሰውነት ሲገባ ደግሞ ህይወት ስለሚዘራ ለማጥፋት ከባድ ነው። በየትም ቦታ የመኖር ባህሪም ስላለውም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው በመንጋጋ ቆልፍ በሽታ ከተያዘ በኋላ የማዳን እድሉ አስቸጋሪ ስለሚሆን ዋናው ሥራ መከላከልን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። ለመከላከልም ህፃናት ከአንድ ዓመት በታች እያሉ ሙሉ ለሙሉ ማስከተብ፣ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቀድመው ቢከተቡ እንዲሁም ነብሰጡሮች ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ በሆስፒታል ቢወልዱ የሚመከር ነው። ክትባቱን መውሰድ ከስጋት ያድናል፡፡

የቲታነስ በሽታን ከሚያመጡ ነገሮች መካከል የዛጉ ብረቶች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው

ምክር፡- ማንኛውንም በቁስ መወጋት የተፈጠረን ቁስለት በተለይ በስራ ላይ በቆሸሹ ቁሶች የሚያጋጥሙንን እንደቀላል ማየት በኋላ ሕይወትን ሊያሳጣ ስለሚችል ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሕክምና በፍጥነት መሄድ ያስፈልጋል፡፡

source ;-http://survival101.info

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *