“ለኦህዴድ የተሰጠው ድርብ ሃላፊነት ነው” – የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ


ለኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦህዴድ) የተሰጠው ድርብ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ገለጹ፡፡

ለቀናት ጥልቅ ግምገማ ሲያካሂድ የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የግንባሩን ሊቀ መንበር መርጧል።

ፕሬዚዳንት ለማ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የኦህዴድ ሊቀ መንበር ዶክተር አብይ አህመድ በኢህአዴግ ምክር ቤት ለግንባሩ ሊቀመንበርነት መመረጣቸው ለድርጅቱ ድርብ ኃላፊነት እንደተሰጠው ያረጋግጣል።

ከግንባሩ ሊቀ መንበርነት ለመልቀቅ የጠየቁትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመተካትና ሊቀመንበሩን ለመምረጥ የነበረው ትግል ዴሞክራሲያዊና እልህ አስጨራሽ እንደነበር ጠቁመዋል።

በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ “ኦህዴድ የተሰጠው ኃላፊነት የኦሮሞ ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንት ለማ፤ መላው የአገሪቷ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኦህዴድን አመራር በመተማመን ኃላፊነቱን በመስጠታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት የተሰጠው ድርብ ኃላፊነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው፤ ኦህዴድ እና የኦሮሞ ህዝብ የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

“የኦሮሞ ሕዝብና የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄዎችን ለመመለስ ቃል በገባነው መሰረት የሚያስፈልገውን መሰዋዕትነት በመክፈል እንሰራለን” ብለዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት መስራት እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *