ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ነገ ይታወቃል ተባለ! እልህ አስጨራሽ ሙግትና ክርክር እየተካሄደ ነው


ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል ተብሎ የሚጠበቀው የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባ እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ የቀጠለ ሲሆን ምርጫው ዛሬ ምሽት ላይ ወይም ነገ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከማክሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ሚስጥር እየተካሄደ ነው የተባለው የግንባሩ ምክር ቤት ስብሰባ እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ ለግምገማ የተዘጋጀ ሰነድን መነሻ ያደረጉ እልህ አስጨራሽ ሙግትና ክርክር እየተካሄዱ መሰንበታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የግንባሩ ሊቀ መንበር ምርጫ ትናንት ይደረጋል የሚል ሰፊ ግምት የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ምንጮች፤ ለውይይት የቀረበው ሰነድ ሰፊ በመሆኑ የሚደረገው ውይይት መጠናቀቅ አለመቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ቀጣዩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል የሚለው አሁንም ከግምት የዘለለ ፍንጭ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ የቀጠለ ሲሆን በም/ቤቱ ከሚካሄዱ ክርክሮች በመነሳት ያልተጠበቀ ሰው ሊመረጥ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የአሜሪካን ድምፅ ያነጋገራቸው የስብሰባው ተሳታፊ ምንጮችም ከግምት ያለፈ ተጨባጭ ማስረጃ ወይም አሳማኝ መሞገቻ ግን አያቀርቡም፡፡ ያልተጠበቀ ሰው ሊመረጥ የሚችልበት እድል መኖሩን፤ ነገር ግን እስካሁን በሊቀ መንበርነት ምርጫው ላይ ውይይት አለመካሄዱን መጠቆማቸው ታውቋል፡፡

የብአዴኑ ሊቀመንበር ምክትል/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ወይም የኦህዴዱ ዶ/ር አብይ አህመድ ሊመረጡ ይችላሉ የሚል ግምት አስቀምጠዋል፡፡ ከግምት ያለፈ ተጨባጭ ማስረጃ ወይም አሳማኝ መሞገቻ ግን አያቀርቡም፡፡ የተለያዩ ግምቶችን እያስተናገደ ከአንድ ወር በላይ በእንጥልጥል የዘለቀው የቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነት ዛሬና ነገ የሚታወቅ ከሆነ፣ ቀጣዩ ቀናት በፓርላማ ቀርቦ፣ ፓርላማው የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝን በክብር አሰናብቶ ፣የአዲሱን ሹመት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ መረጃ፣ ህወሀቶች ዶክተር አቢይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አንዳይሆን የሚታገሉባቸውን ምክንያቶች በግልጽ ማስረዳት ጀምረዋል እየተባለ ነው፡፡ ሚስጥሮች በቀላሉ ከሚያፈተልኩበት ስብሰባ የወጡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከሆነ ዶክተሩ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ የሚደጋግሙት ነገር ለህወሀቶች አልተዋጠላቸውም፤ በጣም የሚገርመው ነገር ይሄንን የሰውየውን ፍቀረ ኢትዮጵያ አቋም አባይ ጸሀዬ እና አስመላሽ ወልደስላሴ የተረዱበት መንገድ ነው፡፡ እንደ ሰዎቹ እምነት ከሆነ የዶክተር አብይ ኢትዮጰያ ላይ መጣበቅ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ወደሌሎቹም ክልሎች እንዲዛመት ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡ ይሄም ማለት አስመላሽ ቃል በቃል እንዳስረዳው ኦሮሚያን ከኢህአዴግ እውቅና ውጪ ከሌሎች ክልሎች ጋር ለማቀራረብ ከተደረገው ሙከራ ለመገንዘብ እንደቻሉት አማራም አንጻራዊ መነቀቃት የፈጠረው (አስመላሽ ያለው ግን የማፈንገጥ አዝማሚያ) ከኦህዴድ የተጋባበት ነው፡፡

እንደ ህወሀቶቹ የመከራከርያ ነጥብ ይሄ ህዝብ ዴሞክረሲ ቀስ እየለ እንጂ በአንድ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ ይሄንን በስብሀት ነጋ፣ በአባይ ጸሀዬ እና በተወሰነ መልኩም በበረከት ስሞን ተደግፎ የቀረበ ሀሳብ ብዙ የብአዴን እና የኦህዴድ ሰዎች የተቃወሙት ሲሆን እንደ አቢይ አህመድ፣ ፍቃዱ ተሰማ እና ገዱ አንዳርጋቸው አምርሮ የተቸ ግን የለም፡፡ ዶክተር አቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት የኢትዮያን ህዝብ ለዲሞክራሲ ባእድ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ አላዋቂነት ነው ብለው ንግግራቸውን ሊቀጥሉ ሲሉ አባይ ጸሀዬ ገና እድሉ እንኳን ሳይሰጠው አቢይ ያቺኑ የገዳ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ምናምን እያልክ በየመድረኩ የምትላትን ነገር ልትደግማት እናዳይሆን በማለት ለማሸማቀቅ ቢሞክርም ዶክተሩ ግን ነግግሩን በመቀጠል እሱ ትልቁ መንገድ ነው- ከዚያ በመለስ እናንተ በወረዳቸሁበት ደረጃ ወርደን አንነጋገር ከተባለ ህዝቡ ዲመክራሲ ትንሽ ትንሽ ሰጥተነው ከሚወቅሰን አብዝተን ሰጥተነው በዛብኝ ብሎን ለምን ታሪክ አንሰራም- ትንሸ ትንሽ የሚባል ዲሞክራሲ የለም ግድየለም አስቲ እኛ ያለገደብ እንስጠውና ትን ይበለው በማለት ተሰብሳቢውን አስቀውታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የራሱን ክልል ስልጣን ብቻ ይዞ በነበረበት ወቅት ውጪ ካሉ ተቃዋሚ ሀይሎች ጋር እንደራደር የሚል ድፍረት የተሞላበት ግብዣ ያቀረበው የአቢይ እና የለማ ቡድን የፌዴራሉን ስልጣን ከያዘ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለስም የሚል ብርቱ ስጋት ህወሀቶች ዘንድ ተፈጥሯል፤ ዶክተሩ የተሸረፈ ስልጣን እንዲወስድ ሲጠየቅም በግልጽ ቋንቋ እኔ የማንም ፍላጎት እና ሀሳብ ማስተላለፍያ ቧንቧ መሆን አልፈልግም- በቀደዱልኝ ቦይ የምፈስ ጎርፍ ሳልሆን የራሴን ፈለግ የምተልም ሰው ነኝ በማለት መናገሩ ደግሞ ፍርሀታቸውን ይበልጥ ጨምሮታል፡፡ ሰዎቹ ሰውየውን አይፈልጉትም፤ አንዳንድ የህወሀት አባላት ደግሞ ዶክተር አቢይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በነበረ ጊዜ ሀገራዊ እርቅ እና ከልብ የሆነ የሰላም ኮንፈረንስ ሊደረግ ይገባል እንዳላቸውና ይህም ጸብ ስለሌለ እርቅ አያስፈልግም ከሚለው የግንባሩ አቋም ጋር እንደሚጋጭ በመጥቀስ ሰውየው እንዳይመረጥ የሚፈልጉበትን ውሀ የማያነሳ ሰበብ ሲዘበዝቡ እንደነበር ተሰምቷል።

በዋናነት ግን በአርብ እለቱ የስብሰባው ውሎ የዶክተሩ መመረጥ እርግጥ ወደመሆን ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሰውየው ከዚህ በኋላ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብሄራዊ ስሜት ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን ስለሚያለያዩን ነገሮች 27 አመታት ሙሉ ስንጮህ ብንቆይም አንድ ስለሚያደርጉን ነገሮች ለመናገር ግን ሰከንዶቸ ክፍለዘመን ሆነውብን ኖረናል አሁን የሄ መቀየር አለበት፡፡ ፓርቲዬ ኦህዴድም የኦሮሞ ህዝብ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ከነፍስ የተሰናሰለ ልባዊ ወንድማማችነቱ እንዲጠናከር ይሰራል፤ ከደም ለሚወፍረው ዘላለማዊ ትስስሩም ያለመታከት በመልፋት አንድነቱን ይንከባከባል- ይሞሽራል በማለት ብዙዎችን ሲያስጨበጭቡ ህወሀቶችን ግን በፍርሀት እና ጥርጣሬ በማኮማተር የሰውየውን ጠቅላይነት አንቀበልም የሚል ሌላ ሀሳብ ይዘው ከምሳ እንዲመለሱ አስገድደዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ህዝብ እንጂ ህወሀቶች ሰውየውን አይፈልጉትም፤ ህወሀት ሆይ በህይወት መንገድ ላይ ሁሌም የሚፈልጉትን ብቻ እያደረጉ ለመቀጠል የህይወት የጫወታ ህግ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ እባክህ ዛሬ እነንኳን ህዝብን ስማና ሰውየውን ዉደድልን፡፡

አዲስአድማስ ጋዜጣ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *