በትራምፕ አንድ የትዊተር መልዕክት አማዞን 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር አጣ


(ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሁን ወቅት ዓለምን በሃብት ብዛት የሚመራ ሰው በባለቤትነት የያዘው አማዞን በትራምፕ የትዊተር መልዕክት ምክንያት 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር እንደከሰረ ተገለጸ፡፡

ትራምፕ በተለመደው የጧት የትዊተር መልዕክታቸው አማዞንን የወቀሱ ሲሆን፥ አብዛኛዎቹን ድርጅቶች ከገበያ አስወጥቷል ብለዋል።

በተጨማሪም የመንግስትን ፖስታ እየተጠቀመ መክፈል የሚገባውን ግብር አልከፈለም ብለዋል በመልዕክታቸው።

ይህንን ተከትሎ ነው ታዲያ በአክሲዮን ገበያ ላይ የኩባንያው ሐብት መጠን በ9 በመቶ የቀነሰው ተብሏል።

የኩባንያ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ የሳምንቱ ኪሳራ ከትራምፕ የተጣራ ትርፍ እንደሚበልጥ ተነግሯል።

በኤንተርኔት በሚደረግ ሽያጭ ግብር ባለመኖሩ ምክንያት እንደ አማዞን ያሉ ድርጅቶች መሰረታዊ የሚባሉ ግብሮችን ሳይከፍሉ ያሻቸውን ይገበያያሉ ነው የተባለው።

የቤዞስ ጠቅላላ ሐብት 107 ነጥብ 7 ቢለየን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል፥ ይህም ዋረን ቡፌትንና ቢልጌትስን በመላቅ ነው በቅርቡ የአንደኝነቱን ቦታ የተረከበው።

ከአንድ ወር በፊት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅዋ ጄነር የስናፕ ቻትን ተንቀሳቃሽ ምስል ተኮር የሆነውን የማህብራዊ ትስስር ገፅን መጠቀም ማቆሟን ተከትሎ በአንድ የትዊተር መልዕክቷ ኩባንያውን 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዳሳጣቸው የሚታወስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *