በግብፅ ሲናይ በመስጊድ ላይ በተፈፀመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 184 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግብፅ ሲናይ ታጣቂዎች በመስጊድ ላይ ጥቃት አደረሱ።

የሀገሪቱ የዜና አገልግሎት ድርጅት እንዳስታወቀው፥ በሰሜናዊ የሲናይ ግዛት በተፈፀመው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትንሹ 184 ደርሷል።

ጥቃቱ በቢር አል አቤድ ከተማ የዓርብ የአምልኮ ፕሮግራም ወቅት ነው የተፈፀመው።

የአካባቢው ፖሊሶችም፥ በአራት ተሽከርካሪ የመጡ ታጣቂዎች ዋናውን መንገድ ለቀው ወደ መስጊዱ በመግባት ፀሎት በማድረስ ላይ በነበሩ አማኞች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

በጥቃቱም ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ125 በላይ ሰዎች ላይም የተለያየ መጠን ያለው የመቁሰል አደጋ መድረሱን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በጥቃቱ ዙሪያ የሀገሪቱን የፀጥታ አካላት ለስብሰባ ጠርተዋል።

ከዛሬው ጥቃት ቀደም ብሎ ከሳምንታት በፊትም ታጣቂዎች በግብፅ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈፅመው በርካታ የሀገሪቱ የጦር አባላት ህይወት ማለፉ ይታወሳል።ከዛሬው ጥቃት ጀርባ የትኛው አካል እንዳለ እስካሁን በግልፅ የታወቀ ነገርም የለም።

ግብፅ በሲናይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አክራሪ እስላማዊ ቡድን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ በመዋጋት ላይ ትገኛለች።ቡድኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት መሃመድ ሙርሲ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሀምሌ ወር 2013 ከስልጣን መውረዳቸውን በሀገሪቱ የተለያዩ ጥቃቶችን እያደረሰ ይገኛል።

ከዚያን ጊዜ አንስቶም በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና ንፁሃን ዜጎች ህይወት ማለፉም ይታወሳል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና ኤፍቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *