በ5 ወር የእርግዝና ጊዜ የተወለደችው ህፃን አሁንም በህይወት ትገኛለች

በ5 ወር የእርግዝና ጊዜ የተወለደችው ህፃን አሁንም በህይወት ትገኛለች

  በሀገረ አሜሪካ በ5 ወር የእርግዝና ጊዜ የተወለደችው ህፃን ሶስት ዓመት በህይወት መቆየቷ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ከመደበኛው የወሊድ ጊዜ አራት ወር ቀድማ የተወለደችው የሶስት ዓመት ህፃን አሁን ባለው መረጃ በዚህ የእርግዝና ወቅት የተወለደች የመጀሪዋ ህፃን ሳትሆን አትቀርም።

ከ22 እስከ 23 የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ ባለው ጊዜ የሚወለዱ ህፃናት በህይወት የመቆየት እድላቸው እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የህክምናው ዘርፍ ተመራማሪዎች ገልፀዋል።

በህይወት የመመቆየት እድል ያላቸው ህፃናት ከ39 እስከ 40 የእርግዝና ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚወለዱ ናቸው።

በአሜሪካ ቴክሳስ በሚገኝ ሆስፒታል በ21 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜ ሴት ህፃን ልጇን ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የወለደችው እናት፥ ሌሎች በዚህ የእርግዝና ጊዜ የወለዱ ሴቶች አሉ ወይ የሚለውን ለማወቅ በኢንተርኔት መረጃዎችን ማፈላለጓን ተናግራለች።

በ22 እና በ23 ሳምንታት የወለዱ ሰዎች ታሪክ ቢኖርም፥ በ21 ሳምንት የወለደች እናት ስለመኖሯ የሚገልፅ መረጃ አለማግኘቷን ጠቁማለች።

በዚህም ምክንያት ልጄ በህይወት አትቆይም የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሮብኝ ነበር ነው ያለችው።

እናት ስቴንሱርድ አዋላጅ ሃኪሟ ከግማሽ ኪሎግራም የምታንሰውን ልጇን በህይወት የመቆየት እድሏ ዝቅትኛ መሆኑን ነግሯት እንደነበርና የህክምና ድጋፍ ቢደረግላት በህይወት የመኖር እድል እንዳላት መጠቆሙን ነው ያስታወሰችው።

የስቴንሱርድ ሴት ልጅ ከመደበኛው የእርግዝና ጊዜ በጣም ቀድሞ በተለይም ከ22 ሳምንት በፊት መወለዷ አዲስ ጉዳይ በመሆኑ ምርምሮች እንዲሰሩ አነሳሽ ሆነዋል።

የህፃኗ ቀለም ከሰማያዊ ቀስ በቀስ ወደ ሮዝ እየተቀየረ መደበኛ የሰው ልጅ መልክ መያዟንም በህክምና ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ህፃኗ በሁለት ዓመት እድሜዋ የአዕምሯዊ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዋ ተመዝኖ የ20 ወራት እድሜ ካለው ህፃን ጋር እኩል ነው ተብሏል።

ሆኖም ቀሪ የአራት ወራቱን ልዩነት በቀጣይ በሚደረጉ የህክምና ድጋፎች ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ነው የተጠቆመው።

በዓለም ላይ ከመደበኛው የመውለጃ ጊዜ ወይም ከ37 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜ ቀድመው የተወለዱ ህፃናት ቁጥር 15 ሚሊየን እንደሚደርስ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *