አስደሳች ዜና ፤ ለጣና!

ከአንድ መቶ ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መሠብሠቡ ተገለፀ!
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ‹‹ዓለማቀፉ የጣና መልሶ ማቋቋም ማህበር ››እንቦጭን ለማስወገድ የሚውል ከ1 መቶ ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ማሰባሰቡን ገለጸ፡፡ በትላንትናው ዕለት ‹‹ጤና ለጣና 2018 ወይም ያለምንም ልዩነት ለጣና ጤንነት›› በሚል መሪ ቃል በዋሽንግተን ዲሲ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ የፕሮጀክቱ መስራችና አስተባበሪ ዶክተር ሶሎሞን ክብረት ከዋሽንግተን ዲሲ እንደገለጹት በዕለቱ ለጣና ጤንነት ወይም ደህንነት የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ከኢትዮጵያውን ዲያስፖራዎች ተሰብስቧል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ የመድሀኒያለም ቤተክርስትያን በበኩሏ በዕለቱ አንድ የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ለመለገስ ቃል ገብታለች፡፡ በርካታ አንጋፋና ወጣት ተወዳጅ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች እና አርቲስቶች በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ መሳተፋቸውን ያስታወቁት ዶክተር ሠለሞን ለዚህ ፕሮግራም መሳካት ለተባበሩትን ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና አስተላልፈዋል። ዓለማቀፉ የጣና መልሶ ማቋቋም ማህበር (Global Coalition for Lake Tana Restoration ) ተጨማሪ ማጨጃ ማሽኖችን ለመግዛትና የሰውሃይል ስልጠና ለመስጠት እንዲሁም የተለያዩ ሃይቁን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ጥናቶችን ለማካሄድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡ ማህበሩ ቀደም ሲል የገዛው የእምቦጭ አረም ማጨጃ ማሽን በቅርቡ ወደ ሃገር ውስጥ ገብቶ ስራ እንደሚጀምር ዶክተር ሠለሞን ለሔሎኢትዮጵያ ተናግረዋል። በማናዬ እውነቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *