ዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዋን በእየሩሳሌም በይፋ ከፈተች


ዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዋን በእየሩሳሌም በይፋ ከፈተች
(ኤፍ.ቢ.ሲ) ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣናቷ በተገኙበት ኤምባሲዋን በኢየሩሳሌም በይፋ ከፈተች፡፡

የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የዋይት ሐውስ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ጃሬድ ኩሽነርና ባለቤቱ ኢቫንካ ትረምፕ ተገኝተዋል፡፡

የኤምባሲው ዝውውር ከተሰማበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ምስራቅ እየሩሳሌምን የወደፊት ዋና ከተማቸው አድርገው በሚያስቡ ፍልስጤማውያን ዘንድ ቁጣ እንደቀሰቀሰ ይታወሳል፡፡

የዛሬው የኤምባሲው የመክፈቻ ስነስርዓት እስራኤል ከተመሰረተችበት 70ኛ ዓመት ጋር መግጠሙ ተነግሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በስነስርዓቱ ላይ በቪዲዮ መልዕክት ንግግር ያደረጉ ሲሆን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ትራምፕ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ነገር እውን ሆኗል ብለዋል እንዲሁም ሀገራቸው የእስራኤል የምንጊዜም ወዳጅ ሆና እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕም በፕሬዚዳንቱ ስም በዚያ ለታደሙት ሰዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ቤተሰብ የተገኘችው ኢትዮ-እስራኤላዊቷ ዘፋኝ ሃሌሉያ የሚል ዘፈን አቀንቅናለች፡፡

የእስራኤል ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልታናት በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሆ ሁሉም ሀገራት የዩናይትድ ስቴትስን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሆኖም የአውሮፓ ህብረት በመግለጫው የኤምባሲ ዝውውሩን አጥብቆ ተቋውሟል፡፡

በርካታ ፍልስጤማውያንም የኤምባሲ ዝውውሩን በማስመልከት የተቋውሞ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ሲሆኑ ዛሬ በተደረገ ተቃውሞ እስከአሁን ከ37 ፍልስጤማውያን በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ
በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *