ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ እጃቸውን በብረት ካቴና እንዳይታሰሩ ጠየቁ

ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ እጃቸውን በብረት ካቴና እንዳይታሰሩ ጠየቁ

  ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ እጃቸውን በብረት ካቴና እንዳይታሰሩ ጠየቁ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው አንጋፋው የተቃዋሚ መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ፍ/ቤት ሲቀርቡ እጃቸው በብረት ካቴና እንዳይታሰርና በማረሚያ ቤት ጎብኚዎቻቸው ብዛት ላይ ገደብ እንዳይደረግ ለፍ/ቤት በጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤ መጠየቃቸውን ጠበቆቻቸው አስታወቁ፡፡
ዶ/ር መረራ እድሜያቸው ወደ 70 ዓመት የደረሰ አዛውንት መሆናቸውን፣ ላለፉት 50 ዓመታትም ለሰብአዊና ህዝባዊ መብት መከበር ሲከራከሩ የኖሩ ፖለቲከኛ እንደሆኑ እንዲሁም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ተማሪዎቻቸው ዘንድ የተከበሩ የቀለም አባት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ፍ/ቤት ሲቀርቡ እጃቸው በካቴና እንዳይታሰር መጠየቃቸውን ጠበቃቸው አቶ ወንድሙ ኢብሳ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የስኳር ህመም ታካሚ በመሆናቸው በብረት ካቴና ሲታሰሩ የሚፈጠረው ቁስለት በጤንነታቸው ላይ አደጋ ስለሚያስከትል፣በካቴና መታሰራቸው እንዲቀር በአቤቱታ ደብዳቤው ጠይቀዋል ብለዋል – አቶ ወንድሙ፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው የህግ ጉዳይ ቢሆንም እጃቸው በብረት ካቴና መታሰሩ ምንም የህግ ድጋፍም ሆነ አሳማኝ ምክንያት የለውም የሚሉት ጠበቃው፤ የማረሚያ ቤቱ አያያዝ በህገ መንግስቱ የእስረኛ አያያዝና የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ መሰረት እንዲሆን ለፍ/ቤቱ ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም በፃፉት የአቤቱታ ደብዳቤ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በማረሚያ ቤት ጠያቂዎቻቸው ብዛት  ላይ ገደብ መደረጉንም አቶ ወንድሙ ይናገራሉ። “ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ 4 ጠበቆች ቢኖራቸውም እኔ ብቻ ነኝ መግባት የሚፈቀድልኝ፤ የቅርብም ሆነ የሩቅ ዘመድ ወዳጆቻቸው ሊጠይቋቸው አይችሉም” ያሉት ጠበቃው፤በጠያቂዎቻቸው ብዛት ላይ ገደብ እንዳይደረግም በደብዳቤያቸው ላይ ጠይቀዋል ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ለፍ/ቤት የሰጡ ሲሆን “ድርጊቱን አልፈፀምኩም፤ጥፋተኛም አይደለሁም” ብለዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም አቃቤ ህግ፣ ምስክሮቹን ለጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም አቅርቦ እንዲያሰማ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የህግ ጠበቃው አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ “የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ስም ዝርዝር ለማወቅ በህግ የተከለከለ ቢሆንም 4 ምስክሮች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተረድተናል” ብለዋል – ለአዲስ አድማስ፡፡   Written by  አለማየሁ አንበሴ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *