ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኬንያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኬንያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለፀ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሀገር ውስጥ እና የጎረቤት ሀገራት ጉብኝቶች አስመልክተው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫ ላይ ነው ይህንን ያስታወቁት።

ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በመግለጫቸውም፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀጣይ የውጭ ሀገራት ጉብኝት መዳረሻ ኬንያ ናት ብለዋል።

በናይሮቢ በሚናራቸው ቆይታም ስኬታማ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ከሀገሪቱ ጋር ከስምምነት ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግብዣ እንደቀረበላቸው ይታወሳል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማን ናቸው በያዝነው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ የግብዣ ደብዳቤውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይዘው የመጡት።

በወቅቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማን በሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት ሀገራት እያደረጉ ባሉት ጉብኝቶች እስካሁን በጂቡቲ እና በሱዳን ስኬታማ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል።

በእነዚህ ሀገራት በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያን ከየሀገራቱ ጋር በኢኮኖሚ የሚያስተሳስሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶች መደረሳቸውም ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማርጊሌህ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በተጨማሪም በመሰረተ ልማት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ እና በውሃ ዘርፍ ያለውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።

በተለይም ኢትዮጵያ የጂቡቲ ወደብ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደመሆኗ የጂቡቲ ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ተደርሷል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር የዶክተር አብይ የሱዳን ጉብኝት ሀገሪቱ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያስመዘገበችበት ነበር እንደነበረ የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።

በተለይም አሁን ካለው የመንገድ መስመር ተጨማሪ ሶስት አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባትና አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያገናኝ የምሰራቅ አፍሪካ ማዕከል የሆነ የባቡር መሥመር ለመዘርጋት ተስማምተዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ በድንበሮች አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠርና የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር የተደረሰውም ስምምነት ሌላው የጉብኝቱ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ አቋም ያላቸውና ግድቡ በተለይም ለቀጣናው አገራት በሚሰጠው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *