ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሱዳን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመለሱ


(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት ጀምሮ በሱዳን ሲያደርጉት የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው ማምሻውን አዲስ አበባ ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፥ በተለያዩ ጉዳዮች ላይም ሀገራቱ ከስምምንት ደርሰዋል።

ሀገራቱ ከተስማሙባቸው መካከል ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ድርሻን በመያዝ ወደቡን በጋራ ማልማት እና ማስተዳደር የሚያስችለው ስምምንት ተጠቃሽ ነው።
የወደብ ልማቱ እና በጋራ የማስተዳደሩ ስራው በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ ሀገራቱ ከስምምነት ደርሰዋል።

የሀገራቱ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር በጋራ ድንበር አካባቢ ነፃ የንግድ እንቀስቃሴ እንዲኖር ሁለቱ መሪዎች ተስማምተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር በተወያዩበት ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር አስፈላጊነት ዙሪያ ገለፃ ያደረጉት ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ያሉትን እንቅፋቶች በማውሰገድ ለጋራ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባም ገልፀዋል።

አክለውም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምታከናውነውን ስራ አጠናክራ ትቀጥላለችም ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈንም ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ ሲሉም ገልፀዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ በቅርበት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

የደቡብ ሱዳን ግጭት እንዲያበቃ በመስራቱ ረገድ ሁለቱ ሀገራት ሀላፊነት እንዳለባቸው በማንሳትም፥ ለሀገሪቱ መረጋጋት ኢትዮጵያ እና ሱዳን በጋራ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያዩ ምክንያቶች በሱዳን እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ያቀረቡትንም ጥያቄ ፕሬዚዳንት አልበሽር የተቀበሉ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት አልበሽርም አስረኞቹ እና ታራሚዎቹ በምህረት እንዲፈቱ ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ አውጥተዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ጉብኝታቸው በሀገሪቱ በግብርና በተለይም በከብት እርባታ ውጤታማ የሆነውን የኦሳማ ዳውድ እርሻን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅትም ኩባንያው በአርሻ እና ከብት እርባታ ዘርፍ በሱዳን መሪ በመሆኑ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *