ፀሎተ ሃሙስ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከብሮ ዋለ


(ኤፍ.ቢ.ሲ) የፀሎተ ሀሙስ በዓል በዛሬው እለት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሮ ውሏል።

በዓሉ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትና በማሰብ ተከብሯል።

ክርስቶስ በዛሬዋ እለት የሃዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ትህትናን እና ታዛዥነት ማስተማሩን በማሰብ ነው በዓሉ የሚከበረው።

በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት በህፅበተ እግርና ሌሎች ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የብፁዕ ጳጳሳቱን እግር፥ ጳጳሳቱ ቆሞሳቱ እና ካህናቱም የምዕመናኑን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክረስቶስን አርአያነት ተከትለው ስርዓቱን የመፈጸሙ ሰነ ስርዓቶችም ተከናውነዋል።

ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልእከት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬዋ እለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ትህትናን እና ታዛዥነትን ያስተማረበት ነው ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ፍፁም ትህትናን እንዳስተማረ ሁሉ ምእመናንም ፍፁም ትህትናን ሊማሩ እንደሚገባም አስረድተዋል።

መቻቻል፣ መከባበር፣ መፈቃቀር እና መተጋገዝንም ከክርስቶስ ልንማር ይገባል ነው ያሉት ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ።

በዓሉ ተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም ብፁእ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን በተገኙበት በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ተከብሯል።።

በተጨማሪም በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል በአሉ ቅባአተ ቅዱሳት የሚባረኩበት ስነ ስርአትም ተካሄዷል።

መእምናንም ቀኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ፍቅርን፣ መቻቻልን እና ትህትናን ያስተማረበት በመሆኑ ሁልገዜም በየእለት ኑሯችን መተግበር አለብን ብለዋል።

በነገዉ እለት የሚከበረዉ የስቅለት በዓልም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን በፆም ፣በስገደት እና በሌሎች ሀይማኖታዊ ስነ ስርአቶች የሚከበር ይሆናል።

በተመስገን እንዳለ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *