ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን በመርታት ለዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋገጠች

ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን በመርታት ለዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋገጠች

 አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2010 ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን በመርታት ከ16 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋገጠች።

በአፍሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ አራት ላይ የተደለደሉት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በደቡብ አፍሪካዋ ፖሎክዋኔ ከተማ በሚገኘው ፒተር ሞካባ ስታዲየም ነው ጨዋታቸውን ያደረጉት።

ከሜዳቸው ውጭ የተጫወቱት ሴኔጋሎች ባፋና ባፋናዎችን 2 ለ 0 ረተዋል።

በዚህም የቴራንጋ አንበሶች ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ ሩሲያ ወደመትስተናግደው የ2018 የዓለም ዋንጫ ማምረቷን አረጋግጣለች።

ጋናዊው የመሃል ዳኛ ጆሴፍ ላምፕቲ በጨዋታ ውጤት ማስቀየር እና ማጭበርበር ላይ ተሳትፈዋል በሚል ይህ ጨዋታ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት ደቡብ አፍሪካ በፖልክዋኔ የፒተር ሞካባ ስታዲየም ላይ በሴኔጋል 2 ለ 0 ተሸንፋ፥ ከዓለም ዋንጫው ውጪ ሆናለች።

በምድቡ አራቱም ሀገራት የማለፍ እድል የነበራቸው ቢሆንም፥ ሴኔጋል አንድ ጨዋታ እየቀራት ከ16 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫው ተመልሳለች፡፡

የሴኔጋልን የድል ግቦች ዲያፍራ ሳኮ እና የባፋና ባፋናው ቶማሳንካ ምኪዝ በራሱ ግብ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥረዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዳካር ላይ የሚገናኙ ይሆናል።

ሴኔጋል እንደ ሳድዮ ማኔ፣ ኬይታ ባልዴ ዲያኦ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ቼክ ኮያቴ እና ሙሳ ሶ የመሳሰሉ ኮከዋክብትን ይዞ ወደ ሩሲያው የ2018 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች።

በምድብ ሁለት ከመርሃ ግብር ማሟያነት በዘለለ የደረጃ ለውጥ በማያስከትለው ጨዋታ ኮንስታንታይን ላይ አልጀሪያ በአዲሱ አሰልጣኝ ራባህ ማጀር እየተመራች ከናይጀሪያ ጋር 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይታለች።

ናይጀሪያ አስቀድማ ወደ ዓለም ዋንጫ ማምሯቷ ይታወቃል።

ጆን ኦጉ ናይጀሪያን ቀዳሚ ቢያደርግም ያሲን ብራሂሚ በፍፁም ቅጣት ምት አልጀሪያን አቻ አድርጓል።

ናይጀሪያ በምድብ ጨዋታዎች ሳትሸነፍ የበላይ ሆና ስታጠናቅቅ በአንፃሩ አልጀሪያ አንድም ጨዋታ ሳታሸንፍ የምድቡ የግርጌ ደረጃን ለመያዝ ተገዳለች።

እስካሁን ሶስት ተሳታፊ ሃገራት ከአፍሪካ ዞን የታወቁ ሲሆን፥ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ግብፅ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራት ናቸው።

ቀሪዎቹ ሁለት ቦታዎች ከቱኒዚያ ወይም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከምድብ አንድ እንዲሁም ሞሮኮ ወይም ኮትዲቯር ከምድብ ሶስት እንደሚያልፉ ይጠበቃል።

የሰሜን አፍሪካዎቹ ቱኒዚያ እና ሞሮኮ ቀሪ ጨዋታዎችን በድል ከተወጡ ወይም አቻ ውጤት ማግኘት ከቻሉ፥ ወደ ዓለም ዋንጫው ሲያመሩ ኮትዲቯር ሞሮኮን ማሸነፍ ብቻ ወደ ዓለም ዋንጫው ይመልሳታል።

ምንጭ፦ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *