መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲኮበልሉ ምን ይዘው ሄዱ ?

መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲኮበልሉ ምን ይዘው ሄዱ ? | መላዕክነሽ ሽመልስ በድሬቲዩብ

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አሜሪካን አገር ኮብልለው በሄዱ ጊዜ መንግሥቱ ኃይለማርያምና፣ፍቅረስላሴ ወግደረስ እየተወያዩ ነበር-አሉ፡፡‹እኔምልህ ጓድ ሊቀመንበር ሰው ሁሉ ኮብልሎ ኮብልሎ እኮ ሁለት ሰው ብቻ ሊቀር ነው› ይላሉ ፍቅሬ፡፡መንጌም በፍጥነት ይመልሳሉ፡፡‹አንደኛው አንተ ነህ፤ሌላው ማን ነው›፡፡

ይህ እንግዲህ በዚያ ሰሞን ከተሰሙ ሹሙጦች አንዱ ነው፡፡የቅኔው ትርጉም፣እኔም በቅርቡ መኮብለሌ አይቀርም ነው፡፡ እውነት ነው፡፡መንጌ ቃላቸውን አላጠፉም፡፡ኮብልለዋል፡፡መጦሪያቸውም ዚምቧብዌ ሆና ቀረች፡፡

ሰሞነኛውን የዚምቧብዌ ፖለቲካ የሚከታተሉ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን የመንግሥቱ ኃይለማርያም ወዳጆች፣ስለቀድሞ መሪያቸው እንደተጨነቁ መደበቅ ተስኗቸው ታይተዋል፡፡አንዳንድ ሰው ይህንን ዓረፍተነገር ካነበበ በኋላ ‹‹መንግሥቱ ደግሞ ወዳጅ አላቸው እንዴ›› ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡‹እንዴታ! ዲያብሎስም እኮ እባብን ወዳጅ አድርጎ ኖሯል›› ብሎ የሚመልስ ደግሞ አይጠፋም፡፡

ለማንኛውም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወልዴ የተባሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዚምቧቤ ወደተባለች አገር ከኮበለሉ 27 ዓመት ሊሞላቸው፣ 159 ቀናት ሲቀሩ ወዳጃቸው ታስሩ፡፡ጋንሒል ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በቅምጥል ኑሮ ጡረታቸውን የሚገፉት ኮሎኔሉ፣ በእውነቱ በሙጋቤ ላይ የደረሰውን ነገር ባዩ ጊዜ መደንገጣቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ አዛውንት የአገሩን መሪ ገርስሶ ከኮበለለ፣ከ43 ዓመታት በኋላ የእርሱ ግፍ በወዳጁ ላይ ሲደርስ ቁጭ ብሎ ያየ ከመንግሥቱ ውጭ ማን ይኖራል?!

የሆነው ሆኖ አዛውንቱ ኮሎኔል፣በሽማግሌው ወዳጃቸው ላይ እየሆነ ያለውን ነገር ከዚምቧብያዊያን እኩል ቢከታተሉት አይፈረድባቸውም፡፡‹እኔ የዚምቧብዌ ሕዝብ እንግዳ እንጂ የሙጋቤ ዕቁባት አይደለሁም›› የሚሉት ኮሎኔል መንግሥቱ፣በውነቱ የሕዝብ እንግዳ መሆናቸው የሚረጋገጥበት ወሳኝ ወቅት ላይ ናቸው፡፡ሁሉንም ነገርም በቅምጥሉ ቤታቸው ውስጥ ሆነው መከታተላቸው የሚጠበቅ ነው፡፡

ለመሆኑ ይህንን ቅምጥል ቤት የሰጧቸው ሙጋቤ ናቸውን? በዕውነቱ እርሳቸውና ወዳጆቻቸው እንደሚሉትስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘውት የወጡት ሃብት የለም ?ለዚህስ ማስረጃው ምንድን ነው?
ጥያቄው በበቂ ማስረጃ ሊፈተሸ ይገባዋል፡፡

በርግጥ መንግሥቱ ኃይለማርያም (ኮሎኔል) ከኢትዮጵያ ይዘውት ስለወጡት ሃብት ሲጠየቁ የሚሰጡት ምላሽ አንድ ነው፡፡
‹‹ ከአገሬ የተረፈችኝ በትረ መኮንኔን ብቻ ነች››

ይህንን የእርሳቸውን ቃል ብዙ ማስረጃዎች ውድቅ ያደርጉታል፡፡ማስረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት ሰውየው እጃቸው የገባላቸውን ሁሉ ዘርፈው እንደወጡም ይሞግታሉ፡፡

መንግሥቱና አጎቱ

መንግሥቱ ኃይለማርያም በጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው አንድ ውሳኔ አሳለፉ፡፡አጎታቸውን አስራት ወልዴን የዚምቧብዌ አምባሳደር አድርገው ሾሙ፡፡ሹመቱ የተጠና ነበር፡፡ይህ ሹመትም ለዛሬው ሰላማቸው ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ስቴፍን ስፔክል የተባለ እስራኤላዊ ደራሲ እንደጻፈው መንግሥቱ አስራትን አምባሳደር አድርጎ ወደ ሃራሬ በመላክ፣ጋን ሒል በተባለ ቦታ መኖሪያ ቤትና የእርሻ መሬት በምስጢር የገዙት ከመሰደዳቸው ጥቂት ወራት አስቀድሞ ነበር፡፡በ1983 መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ የመንግሥቱ ሚስት ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻው ወደ ዚምቧብዌ ተጉዘው ነበር፡፡ጉዞው ምሥጢራዊ ነበር፡፡ዓላማውም የተገዛውን ቤት መጎብኘትና፣ለልጆቻቸው የሚሆን ትምህርት ቤት ማፈላለግ ነበር፡፡

ጉዳዩ ግን እንደተጠበቀው ምስጢራዊ አልሆነም፡፡የዚምቧብዌ ፓርላማ አባላት መረጃውን አገኙት፡፡በፓርላማው ውስጥም ሙጋቤ ተወቃሽ ሆኑ፡፡የአገሪቱን እንደራሴዎች ም/ቤት ሳያማክሩ፣ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ጥገኝነት ልትሰጡ መሆንዎ ተገቢ አይደለም ሲሉም አባላቱ ሞገቷቸው፡፡ኢትዮጵያዊው አምባገነን ግን ወደ ዚምቧብዌ ከመሄድ አልቀሩም፡፡

ታዲያ ምን ይዘው ሄዱ
መንግሥቱ ‹ይዤ የሄድኩት በትረ መኮንኔን ብቻ ነው› ይበሉ እንጂ እውነታው እንደዛ አይደለም፡፡መንግሥቱ ከመሰደዳቸው በፊት፣ከአዶላ ወደ ውጭ የሚላከውን ወርቅ ሸጠው በግል አካውንታቸው ማስቀመጣቸው የማይደበቅ እንደነበር ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ፡፡ሲኤምሲ አካባቢ ለውጭ ሃገር ዲፕሎማቶች ተሰርቶ የነበረውን አፓርታማም ካከራዩ በኋላ ድንቡሎ ሳንቲም ለመንግሥት አላስገቡም፡፡ቤተ እስራኤላዊያን ከአገር እንዲወጡ በመተባበራቸውም ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተከፍሏቸዋል፡፡

በኢዮቤልዮ ቤተመንግሥት ተቀምጠው የነበሩ ዘውዶችን፣ኒሻኖችን፣ወርቆችን፣ከዝሆን ጥርስ የተሰሩ ውድ ጌጣጌጦችንና ለመንግሥት የተሰጡ ገጸ-በረከቶችን በሙሉ ወደ ሃራሬ እንዳሸሹም እንደ ሞሳድ ባሉ የስለላ ተቋማት ተረጋግጧል፡፡

የመንግሥቱን መሰደድ በተመለከተ በወቅቱ ዝርዝር ዘገባ አውጥቶ የነበረው ዘ-ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ እንዳስነበበው፣መንግሥቱ ወደዚምቧብዌ ሲገባ ይዘውት ከነበረው ሶስት ሚሊዮን ካሽ በተጨማሪ፣በሲዊዝ ባንኮች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን አስቀምጠው ነበር፡፡

እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች የመንግሥቱን ኃይለማርያምን ቅምጥል ኑሮ ምንጩን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ጓደኞቻቸው ሁለት አስርታትን ለተጠጋ ጊዜ በእስር ቤት ሲማቅቁ እርሳቸው በምቾት ሲንደላቀቁ ነበር፡፡ሚሊዮኖች በልጆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ሃዘን፣ ዘመን ተሻጋሪ ስቃይ ሲያቆስላቸው፣እርሳቸው ሶስቱንም ልጆቻቸውን ዶክተር አድርገዋል፡፡የዚህ ሁሉ ምንጭ በስልጣን ዘመናቸው ያገኙትና ከዚህ ሕዝብ ጉሮሮ የነጠቁት ሃብት ለመሆኑ ግን መጠራጠር አይቻልም፡፡

ወዳጃቸው ሙጋቤ ግን ለዚህ አልታደሉም፡፡አልጋቸው ላይ ተማርከዋል፡፡የኮሎኔል መንግሥቱ ዕጣፈንታም እስካሁን አልተገመተም፡፡ለዘመናት ‹ወንጀለኛውን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለኢትዮጵያ አሳልፈን መስጠት ስልጣን ብንይዝ የምንፈጽመው ነገር ነው›› ሲሉ የኖሩት ተቃዋሚዎችም ሰሞነኛ እቅዳቸው ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡

 

ይሕንን ጽሁፍ ለመጻፍ የሚከተሉትን መጻሕፍት ተጠቅሜያለሁ፤
ጎቲም ሲሞን-ያየሰው ሽመልስ
አጥፍቶ መጥፋት-ዮሃንስ ሙሉጌታ
Operation Solomon-Stepn Specle

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *