በመዲናዋ እያታለሉ እስከ 5 ሚሊየን ብር ይዘው የሚሰወሩ ወንጀለኞች ተበራክተዋል

በአዲስ አበባ ከእኛ ጋር ብትሰሩ ትርፋማ ትሆናላችሁ እያሉ እያታለሉ እስከ 5 ሚሊየን ብር ይዘው የሚሰወሩ ወንጀለኞች ተበራክተዋል።የሰሜን ሽዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳ ነዋሪው አቶ እሸቱ ገብሬ እንደሚሉት በአንድ ወቅት ከአዲስ አበባ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው።

ስልኩም ከወንድማቸው ልጅ የተደወለ ነበርና የተለመደውን ሰላምታ ተለዋውጠው ለብርቱ ጉዳይ እንደሚፈልጋቸዉ አጫውቷቸዉ ወደ ጉዳዩ ገቡ።ከውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ቤት መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚፈልጉ እና አብሯቸዉ የሚሰራ የአካባቢው ባለሀብት እንደሚፈልጉ አስረዳቸው።

ባለሀብት የተባሉት ግለሰቦች በአካባቢው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች እና የወተት ልማት ያላቸውን ግለሰቦች ቀድመው አጥንተዋል፤ አቶ እሸቱ በወንድማቸው ልጅ የተሰጣቸውን የቤት ስራ ተቀብለው ሰዎችን ማፈላለግ ጀመሩ።አብሮ መስራት የሚኖረዉን ተጠቃሚነት የተረዱት ጎደኛቸውም የአብረን እንስራ ጥያቄውን ሳያቅማሙ ተቀበሉ፤ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን አቶ አሸቱ ይናገራሉ።

“ጓደኛዬ ከውጭ እንመጣለን ከሚሉት ሰዎች ጋር ተዋወቀ፤ ሆኖም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተበደርኩትን 300 ሺህ ብር ገንዘብ ወስደውብኛል አለ፤ እኔ የሰዎቹን ማንነት አላውቃቸውም፤ የማታለል ወንጀሉ ተጠቂ ሆኛለሁ፤ ንብረቴንም እያጣሁ ነው” ይላሉ።በአዲስ አበባ “ከእኛ ጋር ብትሰሩ ከፍተኛ ትርፍ ታገኛላችሁ” በሚል አታለው እስከ 5 ሚሊየን ብር ይዘው የሚሰወሩ ወንጀለኞች እየተበራከቱ መጥተዋል።

አቶ እሸቱን በምሳሌነት አነሳን እንጂ በመዲናዋ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች መበራከታቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

በኮሚሽኑ የከባድ እና ልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ሃላፊ ኮማንደር አበራ ቡሊና፥ እንዲህ ያሉ የማጭበርበር ወንጀሎች ከ1993 እስከ 2003 ዓ.ም ተበራክተዉ እንደነበር ያስታውሳሉ።ከ2003 ዓ.ም በኋላ ግን ፖሊስ እና አቃቤ ህግ ባደረጉት ብርቱ ጥረት እነዚህ አታላዮችን ማዳከም ተችሎ ነበር ።

ሆኖም የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በተለይም በማዕድን፣ በዶላር እና በሌሎች ቁሳቁሶች ተጭበረበርን የሚሉ አቤቱታ አቅራቢዎች እየተበራከቱ መምጣታቸዉን ነው ኮማንደር አበራ የተናገሩት።የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ምንይበል አየነዉ እንደሚሉት፥ በእንዲህ ያለ ተግባር የሚሰማሩ አታላዮች አስቀድመው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ደካማ ጎን ያጠናሉ።

በአብዛኛዉም እንዲህ ያሉ የማታለል ወንጀሎች ሲፈፀሙ ግንኙነቱ የሚጀምረዉ በቤተሰብ እና ታማኝ ጎደኛሞች መሆኑ የጉዳቱ ሰለባዎች እንዳይጠራጠሩ ምክንያት ሆኗል።

በማታለል ወንጀል የተሰማሩ አካላት ለድርድር የሚያቀርቡት ገንዘብ ከፍተኛ ሲሆን፥ ለፖሊስ ኮሚሽኑ አቤቱታቸዉን ካቀረቡ ተጎጂዎች አብዛኛዎቹ፥ ከ3 እስከ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብን በአታላዮች መነጠቃቸውን ኮማንደር አበራ።ይህ አልበቃቸዉ ብሎም ደረቅ ቼክ በማስፃፍ በወንጀል እንዲጠየቁ ከማድረግ ጀምሮ በርካቶች ሀብት ንበረታቸዉን እስከመሸጥ ደርሰዋል።

በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ ግለሰቦች ከቀረበላቸው ማማለያ በመነሳት አብዝቶ ለማትረፍ ወይም በአቋራጭ ለመክበር ካላቸዉ ፍላጎት አንፃር፥ ለቤተሰቦቻቸው እና ለትዳር አጋሮቻቸው መናገር አይፈልጉም ነው የሚሉት ኮማንደር አበራ።በማታለል ወንጀል በተሰማሩ ግለሰቦች ሴራ ውስጥ የገቡ ግለሰቦች መጨረሻቸዉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አለመግባባት ብሎም እስከ ትዳር ፍቺ ይደርሳል።

አብዛኛዎቹ ሚስጥር እንዳያወጡ ወይም ጉዳዩን ለህግ አካል እንዳያቀርቡ በተለያዩ መንገዶች ተጎጂዎችን ያዳክሟቸዋል።
በእንዲህ ያለው ተግባር የተጎዱ ግለሰቦች ብዙዎች ቢሆኑም፥ ጉዳያቸውን አዳባባይ አውጥተው ለህግ የሚያቀርቡት ግን ጥቂቶች መሆናቸውን የተናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ምንይበል አየነው ናቸው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቅርብ ወራት ብቻ እንዲህ ያለ የማታለል ወንጀል ሊፈፀምባቸው የነበሩ ሰዎች ቀድመዉ ለፖሊስ በመጠቆማቸዉ ከ14 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል።የኮሚሽኑ የከባድ እና ልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ሃላፊ ኮማንደር አበራ ቡሊና፥ በዚህ ዓይነት የማጭበርበር ድርጊት ተሳትፈው የተገኙ ግለሰቦችም እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት መቀጣታቸውን ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ ድርጊቱን ፈፅመው የተገኙ ወንጀለኞች ደግሞ ከ15 ዓመት በላይ ተቀጥተዋል።በማታለል ወንጀል የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን በማደን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ነው ኮማንደሩ የገለፁት።

ህብረተሰቡም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከአታላዮች እንዲጠብቅ፥ እንዲህ ያለ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ሲኖሩም ለኮሚሽኑ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

SOURCE FBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *