ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከ”ቀይ ሰይጣንነት” ወደ “ነጭነት” የተቀየረባት ዕለት…#Mensur Abdulkeni

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ
ከ”ቀይ ሰይጣንነት” ወደ “ነጭነት” የተቀየረባት ዕለት

…ረፋድ ላይ። በሊዝበን ከተማ አንድ የግል አውሮፕን ወደ ስፔን ለመብረር ሞተሩን አስነሳ። በጉዞው መዳረሻ ማድሪድ ልዩ ዝግጅት ስላለ በታላቅ ጉጉት ይጠበቃል።

በረራው በ20 ደቂቃ ቢዘገይም ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ 12 ወዳጆቹና የቤተሰቡ አባላት በረራቸውን ወደ ሰሜን አቅጣጫ በማድረግ ጀመሩ።

በትሬሆን ደ አርዶዝ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ የወጣትነት ውበት የተደፋበት ዘለግ ያለው ሮናልዶ ከአውሮፕላኗ ወጣ። የዳይመንድ ሎቲው ጆሮው ላይ ያበራል። በጂንስ ሱሪና ቀይ ጃኬት ደምቋል። ከውስጥ የለበሰው የስፖንሰሩ ናይኪ ምልክት ያረፈበት ነጭ ቲሸርቱ ይታያል። ፀጉሩ ባነሰ መጠን ተቆርጧል። የአውሮፕላኑን ደረጃ እንደወረደ በስፔን ምድር ላይ የመጀመሪያውን አውቶግራፍ ፈረመ፣ ፎቶዎች ተነሳ።

ዛሬ ሰርጉ ባይሆንም “ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ!” ቢዘመርለት አያንሰውም። ወደ ትልቁ ባለታሪክ ሪያል ማድሪድ የሚያደርገው ዝውውር ይፋ የሚሆንበት የደስታው ቀን ነው። ሳንቲያጎ ቤርናቢዩም ሙሽራዋን በጉጉት ትጠባበቃለች።

በቤርናቢዩው የስነስርዓቱ “ካህን” ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ናቸው። የሪያል ማድሪዱ አለቃ በዓለም የተጫዋቾች ክብረ ወሰን የማዴይራውን ልጅ በመጨረሻ ከማንቸስተር ዩናይትድ እጅ ፈልቅቀው ወስደዋል። ይህን ጀብዳቸውን “እወቁልኝ” የሚሉት ደግሞ በዚሁ ስነስርዓት ነው። ለባለትዳሩና ጎልማሳው ፔሬዝም ዕለቱ ከሰርጋቸው ዕለት ደስታቸው ጋር የሚወዳደር ነበር።

…ጠባቂው አጅቦት ወደ ተዘጋጀለት መኪና መራው። መስታወቷ በጥቁር ልባድ የተለበጠ ነጭ ኦዲ መኪና ተዘጋጅታለታለች። በኋለኛው ወንበር በማናጀሩ ዦርጌ ሜንዴዝና በእህቱ ባል ዜ ታጅቦ ጉዞ ተጀመረ።

ሶስቱ ሰዎች በዦርጌ ስፓኒሽ ችሎታ እየቀለዱ፣ ሮናልዶም ረጋ፣ ዘና ብሎ ዋናውን ጎዳና ሲያያዙ ጥቂት ሸለብ አደረገ።

ከፊርማው በፊት በተዘጋጀ ልዩ ክሊኒክ ለህክምና ምርመራ ቆሙ። ከ10 ቀናት በፊት ሮናልዶ በፖርቱጋል ሙሉ ምርመራ ተደርጎለት ለዝውውሩ ብቁ መሆኑ ተመስክሮለት ነበር። ሆኖም በማድሪድም እንደገናም ታየ። ክሊኒኩ ዘንድ ሲደርስ በካሜራዎችና በመቅረፀ ድምፆች ተከቧል። ደጋፊዎችም በብዛት መጥተዋል። አንዲት የ18 ዓመት ኮረዳ “ሮናልዶ እወድሃለሁ!” የሚል ጽሁፍ ይዛ ቆማለች።

ደም፣ ሽንት፣ ኢሲጂ፣ ኤኮካርዲዮግራም፣ ኤምአርአይ፣ የደረት ራጅ፣ የእግር፣ የእጅ ምርመራዎች ተደረጉለት። 30 ደቂቃ የፈጀው ምርመራ ሲያበቃ ጉዞ ወደ ቤርናቢዩ ሆነ።

በመንገድ ላይ የትራፊክ መብራት ሲያቆማቸው ሁለት ወጣት ሴቶች ከየት መጡ ሳይባል መኪናቸው አጠገብ እየጮሁ ቀረቡ።

“ክሪስቲያኖ! ክሪስቲያኖ!” ይላሉ።

ሮናልዶ የመኪናውን መስተዋት አውረዶ “አንሺ! አንሺ! ፎቶውን አንሺ!” ሲል ከሁለቱ አንደኛዋን አበረታታት።

ፎቶ ተነሱ። ከዚያም እጁን አውጥቶ ጨበጣቸው።

“ትውውቁ ላይ እናይሃለን!” እያሉ ደስታቸውን እያጣጣሙ ተሰናበቱትና ጉዞ ወደ ቤርናቢዩ ሆነ።

ነጯ ኦዲ ወደ ቤርናቢዩ መግቢያ ተጠጋች። ክሪስቲያኖ አሳንሰሩን ይዞ ወደ ክለቡ ጽህፈት ቤት አመራ። ረጅሙ ስራ ገና አሁን ተጀመረ። በቅድሚያ የስፔን ጋዜጦችን አሳዩት። በሁሉም የፊት ገፆች ላይ ምስሉ ወጥቷል። ከዚያ በስሙ የታተመውን የመጀመሪያው ማሊያ ላይ ፊርማውን አኖረ። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰሉ ሺሆች የሮናልዶ ማሊያዎች በክለቡ ሱቅ ተቸብችበዋል።

የሪያል ማድሪድ የወቅቱ ጄኔራል ማናጀር ሆርጌ ቫልዳኖ የዕለቱን ፕሮግራሞች ይዘት በቅደም ተከተል አብራራለት። በቢሮው ሰፊ መስኮት በኩል ሜዳው ይታያል። ንግግር የሚያያደርግበት ስቴጅ እየተዘጋጀ ነው። የዝግጅቱ ሽር ጉድ ቀጥሏል።

ከስነስርዓቱ በፊት ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ ቲቪ ጋር ቃለምልልስ አለበት። በግራጫ ሙሉ ልብስ ሩብ ሰዓት በስፓኒሽ፣ ሩብ ሰዓት በእንግሊዝኛ ቃለምልልሱን ከፈፀመ በኋላ ወደ ፕሬዚዳንቱ አመራ።

ፔሬዝ ወደ ስታዲየሙ ንጉሳዊ ትሪቡን ወሰዱት።

“ክቡር ፕሬዚዳንት፣ ዛሬ ጨዋታ አለ አንዴ?” ሮናልዶ ቀለደ። ፔሬዝ በፈገግታ ብቻ መልስ ሰጡት። ሰውየው የዓለማችንን ኮከብ በማግኘታቸው ጮቤ ረግጠዋል። በቦርዱ ጽህፈት ቤት በሞላላው ጠረጴዛ ጎን ከፔሬዝ ጎን ተቀምጦ፣ በአራት ዶሴዎች ላይ የኮንትራት ፊርማውን አኖረ። ፔሬዝም ተመሳሳዩን አደረጉ። በክፍሉ ውስጥ የቀድሞ ዝነኞች አልፍሬዶ ዲ ስቴፋኖ፣ ዩዜቢዮ እና ሌሎች ዳይሬክተሮች “ቀዩ ሰይጣን” ሮናልዶ በይፋ “ነጭ” ሲሆን ተመለከቱት።

ሁሉም አጨበጨበ። የፎቶ ካሜራዎች ታሪካዊ ምስሎችን ለማስቀረት ተንቀጫቀጩ። ፔሬዝ የተፈረመበትን ብዕር፣ የቤርናቢዩን ሞዴል እና አዲስ ሰዓት በስጦታ መልክ አበረከቱለት።

በመልበሻ ቤት በ8 ቁጥሩ ካካ እና በ10 ቁጥሩ ሽናይደር ማሊያዎች መካከል የሮናልዶ 9 ቁጥር ተንጠልጥሎ ባለቤቱን ይጠብቀዋል። ክሪስቲያኖ ሙሉ ልብሱን አውልቆ ነጩን ማሊያ አጠለቀው።

“ነጭ ያምርብሃል ባክህ?!” ፔሬዝ በተራቸው ቀለዱ።

ሮናልዶም ትጥቁን አሳምሮ ወደ መስተዋቱ ቀረበ። ሁሉ ነገር ያምራል። ፎቶዎችን ተነሳ። በቻይንኛ፣ በጃፓንኛ፣ በዓረብኛ ስሙ በተፃፈባቸው ማሊያዎች ፎቶዎችን መነሳቱን ቀጠለበት።

የቢሮው ስነስርዓት ሁሉ ካበቃ በኋላ በሜዳው ዝግጅት ላይ ፔሬዝ ስሙን እስኪያስተዋውቁ ድረስ እንዲታገስና፣ ስሙም ሲጠራ እንዲወጣ ተነገረው። ትዕዛዙም ተቀብሎ ስሙን መጠባበቅ ጀመረ።

የተጠበቀችው አጓጊ ሰዓት ደረሰች።

“ክሪስቲያኖ ሮናልዶ!” ሲባል ፖርቱጋላዊው ኮከብ ከቤርናቢዩ ጉያ ወደ ሜዳው ወጣ። ያን ጊዜ ስታዲየሙ በጩኸት ተደበላለቀ።

“Si, Si, si …Cristiano ya este aqui,” ተዘመረ።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ አቪዬሮ ገና ሳይጫወት ክብረ ወሰን ሰበረ። በ1984 ኔፕልስ ዲዬጎ ማራዶናን ስትቀበል ሳን ፓውሎ በ65ሺ ተመልካች ተሞልቶ ነበር። ያቺ ቀን በእግር ኳሱ ዓለም በአዲስ ፈራሚ ትውውቅ ላይ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር የተመዘገበባት ነበረች። ሮናልዲንሆ በኤሲ ሚላን ሲተዋወቅ 40ሺህ፣ ለካካ በቤርናቢዩ 50ሺህ ተመልካች ተገኝቷል። ሮናልዶ ግን የሁሉንም አስከነዳ። በአንድ ወገን በእድሳት ላይ የነበረው ቤርናቢዩ ያለጨዋታ፣ ለእንኳን ደህና መጣህ ስነስርዓት ብቻ 80ሺህ ተመልካች አስተናገደ። በዚያ ውብ የበጋ ዕለት 5ሺህ የሚጠጉ ማድሪዳዊያን ቲኬት አለቀ ተብለው በአቀባበሉ ላይ ባለመገኘታቸው አዘኑ። ጁላይ 9 ቀን 2009…።

………
የማንቸስተር ዩናይትድ እና የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ይህችን ቀን እንዴት ታስታውሷታላችሁ?

#Mensur Abdulkeni

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *