የከተማን መሬት በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ ሊሻሻል ነው

በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ክለሳ ላይ ዉይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፡ ህዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም
በሀገራችን ሊዝ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ 23 አመታትን አስቆጥሯል፡፡ አሁን ስራ ላይ ያለዉ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገዉ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ሶስተኛዉ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ ሲሆን በስራ ላይ ከዋለ አምስት አመታት ተቆጥሯል፡፡ የአዋጁን መዉጣት ተከትሎ በሀገሪቱ በአብዛኛዉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በዛሬው እለትም የከተማን መሬት በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ክለሳ አስፈላጊነት ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ከሴክተር መስሪያ ቤቶችና ተጋባዥ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አዳራሽ ዉይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱም አዋጁ በሥራ ላይ በዋለባቸው ባለፉት 5 ዓመታት ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረዉን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በሰፊዉ የቀነሰ ቢሆንም ወቅቱ የሚፈልገዉን ልማት ከማምጣትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሙሉ በሙሉ ከማረጋገጥ አኳያ በተለያዩ ወቅቶች በተደረጉ የአዋጁ አፈጻጸም ዳሰሳዎችና የኦዲት ግኝቶች መሰረት በአዋጁ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ይህን አዋጅ መከለስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡
በመሆኑም በሊዝ አዋጅ 721/2004 ላይ የተስተዋሉ ዋና ዋና ክፍተቶች ተለይተዉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ ማሻሻያ ሃሳቦች በሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ እንዲካተቱ ተደርጓል ያሉት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ናቸው፡፡ በሊዝ አዋጅ 721/2004 ያጋጠሙ የህግ ክፍተቶች እና የአፈጻጸም ችግሮችን በመለየት ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ዉይይት ማድረግ ጉድለቶችን ለመሙላት እንደሚረዳ የገለፁ ሲሆን የሊዝ ስርዓቱን ይበልጥ ዉጤታማ ለማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነት መንገድን የሚዘጉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑ እና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ አንቀጾች በተከለሰው አዋጅ ስር መካተቱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከህብረተሰቡ ቅሬታ ሲነሳባቸው በነበሩ ጉዳዮች እንዲሁም ነባሩ የሊዝ አዋጁ ያልሸፈናቸዉ እና ወቅቱ የፈጠራቸዉ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ሲባል አዋጁን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለውናል፡፡
በዉይይቱ ላይ የተከለሰው አዋጅ የቀረበ ሲሆን ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ፣ ሁሉንም ከተሞች ወደ ሊዝ ለማስገባት ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉ፣ ያለ ፈቃድ የተያዙ ይዞታዎችን ስርዓት ለማስያዝ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ በማለቁ ተጨማሪ የጊዜ ገደብ እንዲጨመር መደረጉ፣ በጨረታ ሰነድ ሽያጭ ላይ አንድ ተጫራች በአንድ የጨረታ ዙር ለተመሳሳይ አገልግሎት ከአንድ ቦታ በላይ መወዳደር እንዳይችል ማድረጉ፣ ለልማት መስኮች የምደባ ቦታ አሰጣጥ ላይ ለክልሎች እና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በማያሻማ መንገድ በግልጽ በማሻሻያ በአዋጁ እንዲቀመጥ መደረጉ፡፡ የስራ ጫና ለመቀነስ እንዲያስችላቸዉ የክልል ካቢኔዎች ለከተሞች ዉክልና የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲኖር መደረጉ፣ ልዩ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸዉ ፕሮጀክቶች የሚዉሉ ቦታዎች እና የከተሞችን የልማት ፍላጎት እና የእድገት ደረጃ ያገናዘበ እንዲሆን የሚሉት በረቂቅ በአዋጁ በግልጽ ከተካተቱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ታጥረው የሚቀመጡ ቦታዎችን ለማስቀረት እና አልሚዎች በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገቡ የሚያደርግ አስገዳጅ ድንጋጌ እና ግንባታን በግማሽ ሳያጠናቅቁ ወደ ሶስተኛ ወገን ማስተላለፍን ለማስቀረት የሚያስችል ህግም እንዲሁ በአዋጁ ተካቷል፡፡
በመጨረሻም ከዉይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ወጥ የሆነ የሊዝ ክፍያ አሰባሰብ ስርአት ያለመኖሩ፣ ለልማት ተነሺዎች በምትክ የሚሰጡ ቦታዎች በግልፅ ቢቀመጥ፣ ከዘርፉ የሚሰበሰበው ገቢ ከ80 በመቶ በላይ ለመሬት ልማት ቢውል የሚሉና ከሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በሀላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የተከለሰው አዋጅ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *