ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሬ

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሬይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሬ / ጫሊ በላይነህ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለጤናዎ እንደምን ሰንብተዋል? በኢህአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው ሀይለኛ ሽኩቻ፣ እርስ በርስ ያለመተማመን ፓለቲካ ከመጠለፍ ተርፈው የኢትዮጽያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለመሀላ በመፈፀምዎ እንደማንኛውም ኢትዮጽያዊ የተሰማኝን ደስታ ልገልፅልዎ እወዳለሁ።

እርግጥ ነው፣ ድርጅትዎ ኢህአዴግ ለዓመታት በሕዝብ ሲጠየቅ የነበረውን የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት፣ የዴሞክራሲ፣ የሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የእኩል ተጠቃሚነትና የሥራአጥነት ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ ሕዝባዊ ቁጣ የገነፈለበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ወደ ሥልጣን መምጣትዎ በአንድ በኩል ከባድ ፈተና ሲሆን በሌላ በኩል በጥንቃቄ ከሕዝብ ጋር ተናበው መራመድ ከቻሉ አጋጣሚው መልካም ዕድልም እንደሚሆን እረዳለሁ።

ክቡር ጠ/ ሚ ከተሾሙበት ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ በሚቀጥሉት 100 ቀናት ቅድምያ ሰጥተው ቢተገብሯቸው ከአገራዊ ጥቅም አንፃር ትልቅ ፋይዳ አላቸው ያልኩዋቸውን የሚከተሉትን 12 ነጥቦች እንደሚከተለው አስፍሬያለሁ።

ዋናውና ትልቁ ነጥብ የወረቀት ላይ ጌጥ እንደሆነ የሚነገርለት ሕገመንግሥታችን ሙሉ በሙሉ እንዲከበርና እንዲተገበር ካብኔዎ የማያወላውል ቁርጠኛ አቋም ሊይዝ ይገባል። ቀጥሎ የማነሳቸው ብዙዎቹ ነጥቦች በቀጥታ በኢትዮጽያ ሕገመንግሥት ውስጥ የተደነገጉ ግን ደግሞ በአፈፃፀም የሚሸራረፉ ናቸው። እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።

1. የፓለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣

በአገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የተቋቋሙ እና በውጭ ሀገር ነፍጥ ያነሱ ተቃዋሚዎች ጭምር ያካተተ ብሔራዊ የዕርቅና የሠላም ጉባኤ ይጥሩ፣ ያገባኛል የሚል
ወገን ሁሉ በአገሩ ፓለቲካ እንዲሳተፍ ይፍቀዱ፣

2. ለዲያስፖራ ወገኖች፣

በውጭ አገር የመንግሥት ተቃዋሚ ሆነው ወይንም ፈርተው ወደአገራቸው መመለስ ላልቻሉ ኢትዮጽያዊያን ወደአገራቸው ገብተው እንዲሰሩ፣ እንዲኖሩ፣ በሁሉም መስክ እንዲሳተፉ ወገናዊ ጥሪ ያስተላልፉ፣

3.የዴሞክራስያዊ መብቶች፣

የመሰብሰብ፣ የመደራጀት ሕገመንግሥታዊ መብቶች ላይ ገደብ የሚጥሉ ልማዳዊ አሠራሮች ኢ-ሕገመንግሥታዊ መሆናቸውን ተረድተው ያንሱ፣

4. እስረኞችን መፍታት፣

በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የተለያዩ የወንጀል ክስ እየተፈበረከ በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ይፍቱ፣

5. የባለሥልጣናት ሐብት ይታወቅ፣

የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች የተመዘገበ ሐብት ለሕዝብ ይፋ ያድርጉ፣ ከገቢያቸው በላይ ሐብት ያፈሩ ባለሥልጣናትን ለፍርድ ያቅርቡ፣

6. ሞሳኝ ሹመኞች ይመንጠሩ፣

በሕዝብ ዘንድ በሙስና የሚጠረጠሩ ባለሥልጣናት ላይ ፖሊስ ምርመራ እንዲጀምር ይዘዙ፣ በአጥፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይውሰዱ፣ ያስወስዱ፣

7. ኘሬስን ይደግፉ፣

የተዳከመው ኘሬስ እንዲያንሰራራ ይደግፉ፣ ኘሬሱ ግልጽና ግልጽ ካልሆኑ ተፅዕኖዎች ይታደጉ፣

8. የንግድ ሥርዓቱን ይፈትሹ፣

በኢኮኖሚው እንደ ኤፈርት ያሉ የኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅቶች፣ እንደሜቴክ ያሉ ተቋማት የንግድ ተሳትፎ ይገድቡ፣ ቢቻል ከንግዱ ያስወጡ፣

9. የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የማያዳግም እርምጃ ይውሰዱ፣

ኮንትሮባንድ ሕጋዊ ንግድን በማዳከም መንግሥት ከታክስና ግብር ማግኘት ያለበትን ገቢ የሚያሳጣ፣ ሕጋዊ ነጋዴዎችን በመጉዳት የንግድ ሥርዓትን የሚያዛባ ነውና እርምጃው ከታይታና ከወሬ የዘለለ እንዲሆን ሊሰራ ይገባል።

10. ሥራ አጥነትን የሚቀርፍ መላ ይፈልጉ፣

ሥራ አጥነት የወጣቶች ቁጣን ያቀጣጠለ ማህበራዊ ችግር ነው። እስካሁን ኢህአዴግ ተኮር አደረጃጀቶችን ተከትሎ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ችግሩን ለመቅረፍ ቢሞከርም ብዙሀኑን ወጣት የሚጠቅም አልሆነም። ይህን ችግር በጥናት በመፈተሽ አስቸኳይ መፍትሄ ያስቀምጡ፣

11.አጥፊዎች ለፍርድ ይቅረቡ፣

በተለይ ሶስት ዓመታት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የታየውን የሕዝብ ቅሬታ ተከትሎ ሠላማዊ ዜጎች ( ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ) ተገድለዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬም ተፈናቅለዋል። በዚህ ሒደት ተካፋይ የነበሩ አካላትን ለፍርድ የማቅረብ ጉዳይ፣ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ጉዳይ መንግሥት ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት አለመፈፀሙ ይታወቃል። ይህን ችግር በፍጥነት ይቅረፉ፣

12. የአስቸኳይጊዜ አዋጁ ይነሳ፣

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት ጠቀሜታ እንዳለው ባይካድም በተቃራኒው አለም አቀፍ ግንኙነትን፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፍን ያሽመደምዳል። ስለሆነም አዋጁ ከተቀመጠለት ጊዜ በፊት እንዲነሳ ቢያደርጉ አገርና ሕዝብ ይበልጥ ይጠቀማል።

በመጨረሻም መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታለሁ!DireTube

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *