ጄሶን ከጤፍ ጋር በመቀላቀል እንጀራ ጋግረው ሲሸጡ የተያዙ ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አያት ኮንዶሚኒየም ጄሶን ከጤፍ ጋር በመደባለቅ እንጀራ ጋግረው ሲሸጡ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እና እያንዳንዳቸው በ15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጡ።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሽ መንግስቱ አንተነህ እና መቅደስ ጋሻው የተባሉ ግለሰቦች ወንጀሉን ከሰኔ 2 ቀን 2009 እስከ ሀምሌ 21 ቀን 2009 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ፈጽመውታል።

በእነዚህ ጊዜያትም ግለሰቦቹ ያልፀና ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው፥ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 10 ልዩ ቦታው አያት ኮንዶሚኒየም ጄሶን ከጤፍ ጋር በመደባለቅ እንጀራ በመጋገር አከፋፍለዋል።

ድርጊቱን በቅርበት ከሚያውቁ የህብረተስብ ክፍሎች በደረሰ ጥቆማ ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር አውሏል።

በዚህም አቃቤ ህግ ተከሳሸሉቹ ላይ ጤናን የሚጎዱ የተበላሹ እቃዎችን እና ምግቦችን በማዘጋጀት እና የጸና ንግድ ፍቃድ ሳይኖር የንግድ ስራ ማከናወን ወንጀል ክስ መስርቶባቿል።

ተከሳሾቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የተቦካ ሊጥ እና ከተጋገረ እንጀራ ላይ ናሙና በመውሰድ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ ጄሶ እንደተቀላቀለበት መረጋገጡን አቃቢ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ቀርበው ክሱ ተነቦላቿል።

ተከሳሾቹ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃልም የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው ክደው የተከራከሩ ሲሆን፥ አቃቤ ህግም ለወንጀሉ ድርጊት መፈጸም ያስረዳልኛል ያላቸውን የላብራቶሪ ምርመራ ውጤት፣ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በዚህም ተከሳሾቹ ከአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በእርከን 31 መሰረት ሁለት ማቅለያ እና ሁለት ማክበጃ ተይዞላቸው በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።

በታሪክ አዱኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *