የተሰጥኦ ባለፀጋ፣ የቅፅል ስም ሃብታም


‘Ronaldinho is coming! [Countdown: 20 Days]

የተሰጥኦ ባለፀጋ፣ የቅፅል ስም ሃብታም

… ዛሬ በመላው ዓለም መለያ መጠሪያው ይሁን እንጂ ብራዚላዊያን “ሮናልዲንሆ” በሚለው ስም አያውቁትም ነበር። “ኦርጂናሉ” ሮናልዲንሆ ትልቁ ሮናልዶ ነው። “ኤልፌኖሜኖ” በሚለው ቅፅል የሚታወቀው ሮናልዶ።

ብራዚላዊያን ስመ ረጃጅሞች ናቸው። ግን በስያሜ አጠራር ጣጣ አይወዱም። ባጭሩ መጥራት ይቀናቸዋል። የቀድሞ መሪያቸውን “ሉላ” ይሏቸዋል። ባለብዙ ጅራቱ የባህር እንሰሳ “ስኩዊድ” የሚል ትርጉም ይኑረው እንጂ “ሉዊዝ ኢግናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ” እያሉ ጊዜ ማባከን አይፈልጉም።

“ሮናልዶ ሉዊዝ ናዛሪዮ ደ ሊማ” ከማለት ይልቅ “ሮናልዶ” የሚቀላቸውም ለዚህ ነው። ግን ሁለት ድንቅ ሮናልዶች በአንድ ዘመን ተገኙና ብራዚላዊያን ግራ ገባቸው።

ያ ታላቅ ጎል አግቢም “ሮናልዲንሆ” ተብሎ በሚጠራበት ሃገር ሌላ “ሮናልዲንሆ” የተባለ አስገራሚ ተጫዋች ብቅ አለ። ትርጓሜው “ትንሹ ሮናልድ” እንደማለት ነው። ኤልፌኖሜኖ “ትንሹ” መባሉ አብቅቶ በዝናም፣ በክብርም ሲያድግ ብራዚላዊያን ወደ “ሮናልዶነት” አሳደጉት።

“ትንሹ” ግን “ትልቅ” ሳይባል የቅፅል ስም ሃብታም እንደሆነ ከኳስ ዓለም ተገልሏል። ሮናልዲንሆ በግሬሚዮ ሳለ ይታወቅ የነበረው “ሮናልዶ” በሚል አጭር መጠሪያ ነበር። በክለብ ታዳጊና ወጣት ቡድኖችም በዚሁ ቀጥሎ ችሎታው እየጎለበተ ሲመጣ “ኢንሆ” ተጨመረለት። “ሮናልዲንሆ” ተባለ። በፖርቱጊዝ “ኢንሆ” ሲጨመርበት “ትንሹ” የሚለውን ቃል በቅድመ ቅጥያነት ያስከትላል። ስለዚህ “ሮናልዲንሆ” “ትንሹ ሮናልድ” ማለት ይሆናል።

ይሁን እንጂ በችሎታ ሲያድግ “ትንሹ” የሚለው የተቀጠለለት ከትልቁ ሮናልዶ ብቻ ሊለዩት ታስቦ አይደለም። በግሬሚዮ በ1980ዎቹ ሌላ ሮናልዶ ይጫወት ነበር። የመስመር ተከላካዩ “ሮናልዶ አልቬስ” ይባል ነበር። ተዓምረኛውን ልጅ ሲያገኙ ደጋፊዎች “ትልቁ” እና “ትንሹን” ለመለየት ሲሉ “ኢንሆን” ጨመሩለትና “ሮናልዲንሆ” ተባለ።

ዝነኞቹ ሮናልዲንሆዎችን መለየት ግን ለብራዚላዊያን አስቸጋሪ ነበር። የኢንተር ሚላኑ አጥቂ ዓለም “ሮናልዶ” እያለው እንኳን በሃገሩ “ሮናልዲንሆ” መባሉን ቀጥሎ ነበር። ስለዚህ የግሬሚዮ ክለብ መቀመጫ በሆነችው ፖርቶ አሌግሬ የሚታተመው ኮሬኦ ዶ ፖቮ ጋዜጣ ሁለቱን የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች “የእኛው” እና “ሌላው” በማለት ይለያቸው ነበር።

ሮቤርቶ ካርሎስ ደግሞ መፍትሔ አለኝ ብሎ ሮናልዲንሆን “አስቀያሚው” የሚል ቅፅል አወጣለት። ብራዚል ከሜክሲኮ ሲጫወቱ ሮናልዲንሆ ተጠባባቂ ነበር። ብዙ የተወራለትን ተጫዋች በሜዳ ለማየት የጓጓው ተመልካች “ጎውቾ! ጎውቾ! ጎውቾ!” በማለት ዘመረለት። የተወለደበት ክልል ስም መሆኑ ነው። ከዚያ ጨዋታ በኋላ ደጋፊዎች ለድንግርግሩ መፍትሔ አገኙለት። “ሮናልዲንሆ ጎቾ” በሚለው መለየት ጀመረ። “ጎንደሬው እገሌ” ወይም “ወሎየው እገሌ” እንደማለት ነው።

ኳስ በነካ ቁጥር ኮሜንታተሮች “ሮናልዲንሆ ጎቾ” ሲሉት ትልቁ ደግሞ ዓለም በሚጠራው “ሮናልዶ” ተባለ። “ኦ” ከተጨመረበት “ትልቁ” የሚለውን ያስከትላል። “ሮናልድ” + “ኦ” = ሮናልዶ (ትልቁ ሮናልድ)።

የሮናልዲንሆ እናት ደግሞ “ናልዶ” እያሉ በቤት ስሙ ይጠሩታል። ትምህርት ቤት “ኮሜዶር ዶ ራቶን” ይባላል። “አይጥ ፊት” ማለት ነው። በእነዚያ የሾሉ ገጣጣ የፊት ጥርሶቹ ምክንያት በአሽሙረኛ ተማሪዎች የወጣለት ቅፅል ነው። አንዳንድ ጓደኞቹ ደግሞ “ዴንቴ” ይሉታል። “ጥርሶ” እንደ ማለት ነው። የግሬሚዮ ተጫዋቾች ሌላ ስያሜ አላቸው። “ሎባኦ”። “ተኩላው” የሚል ትርጉም ይሰጣል።

በፓሪስ ፈረንሳዊያኑ “ኢንሆ” የሚለው ቅጥያ ለአነጋገር ስለከበዳቸው “ሮኒ” ብለው አሳጠሩት። ወደ ባርሴሎና ብትሄዱ “ዲንሆ” በሚለው የፍቅር ቅፅል ይታወቃል። የአርጀንቲና ኮሜንታተሮች “ጃህ ጃህ ቢንክስ” በተባለው የስታር ዋርስ ፊልም የሳይንስ ልብወለድ ፍጡር ሰይመውታል።

የቅፅል ስሙ ጋጋታ ማንነቱን አይቀይረውም። በእነዚያ የላ ሊጋ ምሽቶች እንቅልፋችንን ከአይኖቻችን ሽፋሽፍቶች ላይ አባሮ በላቀ ቴክኒካዊ ግርማ ሲያስገርመን ለነበረው የባርሴሎና 10 ቁጥር ሌላ ማንነት አይሰጠውም። ስምንት ቅፅል ቢኖረው ስምንት ዲንሆ የለም። There is only one Ronaldinho Gaucho de Assis Moreira!

……..
#HeinekenEthiopia
#ShareTheAction
#MeetTheLegend
#Bisratsport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *